Wednesday, October 30, 2024

ደንበር አቋርጠው በአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ የሙርሌ ታጣቂዎችን ለመከላከል እንዲያስችል የፀጥታ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ አሳሰቡ፡፡ ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተመልምለው በኢታንግ ልዩ ወረዳ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ 810 ያህል የሚሊሻ አባላት ተመርቀዋል፡፡

አባላቱ ላለፉት 34 ቀናት የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችንና የክፍል ውስጥ ትምህርትን በመውሰድ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ አባላት ናቸው ለምርቃት የበቁት፡፡ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶማስ ቱት እንደገለፁት በክልሉ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ሰላማቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ለማስቻል ዘርፉን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት የሚሰሩ የሚሊሻ አባላትን አሰልጥኖ አካባቢያቸውንና ድንበራቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ለአብነትም ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ ባስተላለፉት መልእክት በተደጋጋሚ ጊዜ ጠረፋማ አካባቢዎች ላይ የሙርሌ ጎሳ አባላት የሚያደረሱትን ጥቃት ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ የክልሉ መንግስት እየሰራበት ነው ብለዋል፡፡

በተለይም አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ላይ የሚደርሰውን ሰዕባዊና ቁሳዊ ጥፋትን ለመከላከል የሚሊሻ አባላት ሰልጥነው ወደ ስራ መግባታቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያቃልለዋል ብለዋል፡፡

የሚሊሻ አባላትን ማሰልጠን ያስፈለገው የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላት በፍጥነት የማይደርሱባቸውን አካባቢዎች ለመቆጣጠርና መረጃ እንዲሰጡ ለማስቻል መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዘውውርን ከመቆጣጠር እንዲሁም በአርሶና ከፊለ አርብቶ አደሩ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል እንዲቻል የፀጥታ አካላቱ በሃላፊነት እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡

የክልሉን ሰላም በይበልጥ ለማጎልበትም የፀጥታውን ዘርፍ የክልሉ መንግስት በመደገፍ የዜጎችን ሰላም በማስጠበቁ ረገድ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ ተመራቂ የሚሊሻ አባላቱ እንዳሉት በተግባርና በክፍል ውስጥ ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ የመጡበትን አካባቢ በፍህታዊ መንገድ እንደሚያገለግሉ አረጋግጠዋል፡:

0 Comments

Leave a Comment